እስልምና እና ሙስሊሞች መረዳት

እስላም ምንድነው?

ሙስሊሞች እነማን ናቸው?

ሙስሊሞች በምን ያምናሉ?

እንዴት አንድ ሰው ሙስሊም ይሆናል?

“እስላም” ምን ማለት ነው?

እስላም ለምንድነው የተለየ የሚመስለው?

እስልምና እና ክርስትና የተለያየ መሰረት ያላቸው ናቸውን?

ቃባ ምንድንነው?

መሀመድ ማነው?

መሀመድ እንዴት ነብይ እና የአምላክ መልዕክተኛ ሊሆን ቻለ?

የእስልምና መስፋፋት እንዴት በአለም ላይ ተፅዕኖ አደረገ?

ቁርዐን ምንድን ነው?

ቁርዐን ስለምን ነው?

ቅዱስ የሆኑ ሌሎች መዛግብቶች ይኖራሉን?

የእስልምና “አምስቱ” ምሰሶዎች እነማን ናቸው?

እስልምና ከሌሎች እምነቶች ጋር ይቸቻላልን?

ሙስሊሞች ስለ እየሱስ ምን ያስባሉ?

በሙስሊሞች ዘንድ ቤተሰብ በጣም አስፈላጊ ለምን ሆነ?

ስለ ሙስሊም ሴቶችስ?

ሙስሊም ከአንድ በላይ ሚስት ሊኖረው ይችላልን?

የእስልምና ጋብቻ እንደ ክርስቲያኖች ጋብቻ ነው?

ሙስሊሞች እንዴት በዕድሜ የገፉ ሰወችን ይንከባከባሉ?

ሙስሊሞች ሞትን እንዴት ይመለከቱታል?

እስልምና ስለ ጦርነት ምን ይላል?

ስለ ምግብ ምን ይላል?

እስልምና እንዴት ለሰብዐዊ መብት ጠበቃ ይቆማል?

እስልምና በአሜሪካ ውስጥ

የሙስሊሙ አለም


እስላም ምንድነው?

እስልምና አዲስ ሀይማኖት ሳይሆን፣ አምላክ በሁሉም ነቢያቶች በኩል ለእያንዳንዱ ህዝብ የገለጸው አንድ እውነት ነው:: ለአንድ አምስተኛው የአለማችን ህዝብ፣ እስልምና ሀይማኖታቸውና የህይወታቸው መንገድ ነው:: ሙስሊሞች የሰላም፣ የምህረትና የይቅር ባይነት ሀይማኖትን ይከተላሉ:: አብዛኛው የእምነቱ ተከታይም እምነቱን አስታክኮ ከሚከሰቱ አንዳንድ ድርጊቶች ላይ ምንም አይነት ነገር አያገናኛቸውም::


ሙስሊሞች እነማን ናቸው?

አለት ዶም ከኢየሩሳሌም ውጭ እጸልይ ሙስሊሞች.
በጸሎት ውስጥ አንድ የሞሮኮ.

በመላው አለም ከአንድ ቢሊዮን ህዝብ በላይ ከተለያየ ዘር፣ ዜግነት እና ባህል ከደቡባዊ ፊሊፒንስ እስከ ናይጄሪያ _ በእስልምና ሀይማኖታቸው ህብረት ያላቸው ናቸው:: ወደ 18% የሚሆኑት የእምነቱ ተከታዮች በአረቡ አለም ይገኛሉ፣ በአለም የብዙ ሙስሊም ማህበረሰብ መገኛ ሀገር ኢንዶኔዥያ ነች፣ ጥቂት የማይባሉ የኤሽያ እና አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ሙስሊሞች ናቸው፣ እንዲሁም ቀደምት የሩስያ ግዛቶች በርካታ ሙስሊሞች የሚገኙበት ሲሆን ጥቂት በማይባል መልኩ በቻይና በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፣ እንዲሁም በአውሮፓ ይገኛሉ::


ሙስሊሞች በምን ያምናሉ?

ሙስሊሞች የሚያምኑት በአንድ፣ ልዩ በሆነ፣ በማይነጻጸር አምላክ፣ በእርሱ በተፈጠሩት መላዕክቶች፣ የእርሱን ራዕይ ወደ ሰው ልጅ ባመጡት ነብያት፣ በመጨረሻዋ የፍርድ ቀንና ለድርጊቶቻቸው ባለው ግላዊ ተጠያቂነት፤ በሰው ልጅ ዕጣፈንታ እና ከሞት በኋላ ባለው ህይወት ላይ በአምላክ ፍጹም ስልጣን ሁሉ ያምናሉ ፤ ሙስሊሞች በነብያት የሚያምኑ ሲሆን በተዋረድም በአዳም በእነ ኖህ፣ በአብርሀም፣ በእስማኤል፣ በይስሀቅ፣ በያዕቆብ፣ በእዮብ፣ በሙሴ፣ በአሮን፣ በዳዊት፣ በሰሎሞን፣ በኤልያስ፣ በዮናስ፣ በመጥምቁ ዩሀንስ እንዲሁም በእየሱስ፣ ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁንና ያምናሉ:: ግን ለሰው ልጆች በአምላክ የመጨረሻዋ መልዕክት፣ የዘላለማዊ መልዕክት ማረጋገጫ እና ከዛ በፊት የሆነው ሁሉ ማጠቃለያ የሆነው በገብርኤል በኩል ለነብዩ መሀመድ በተገለጸው ነው::


እንዴት አንድ ሰው ሙስሊም ይሆናል?

በቀላሉ ለመናገር “ከአምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም እንዲሁም መሀመድ የአምላክ መልዕክተኛ ነው” በማለት ይሆናል

ይህን በማወጅም አማኙ የእርሱ ወይም የእርሷ እምነት በሁሉም የአምላክ መልዕክተኞች እና ባመጧቸው ቅዱስ መጽሀፍት ይሆናል::


“እስላም” ምን ማለት ነው?

የአረብኛ ቃሉ “እስላም” እንዲሁ ሲተረጎም “መማረክ” ማለት ነው፣ ስረ ትርጉሙም “ሰላም” ከሚል ቃል የመጣ ነው፤ በሀይማኖታዊ አተረጓጎም ለአምላክ ፍጹም ምርኮኛ መሆን እንደማለት ነው:: “መሀመዳኒዝም” (መሀመዳዊያን) የሚለው አገላለጽም ፍጹም የተሳሳተ ነው ምክንያቱም ሙስሊሞች ከአምላክ ይልቅ መሀመድን የሚያመልኩ ያስመስላልና ነው:: አላህ ማለትም አምላክ ለሚለው የአረብኛ ስሙ ነው፣ ይህም በአረብ ሙስሊሞችም ሆነ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚጠቀሙበት ነው::


እስላም ለምንድነው የተለየ የሚመስለው?

እስልምና በዘመነኛው አለም ልኬት የባዕድ ወይም ጽንፈኛ ሊመስል ይችላል:: ምናልባትም ይህ የሆነው በምዕራቡ አለም ሀይማኖት ከዘወትር ተግባር ጋር ቁርኝት ስለሌለው ሲሆን፣ በሙስሊሞች ዘንድ ግን ሁሌም በአዕምሯቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ነው፣ እንዲሁም በአለማዊ እና በመንፈሳዊ መንግስት መካከል ክፍፍል አይፈጥሩም:: መለኮታዊ የሆነው የሸሪያ ህግ በጽኑ ይተገበር ዘንድ ያምናሉ፣ ለዚህ ነው ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በጣም ጠቃሚ የሆኑት::


እስልምና እና ክርስትና የተለያየ መሰረት ያላቸው ናቸውን?

አይደሉም:: አይሁድን ጨምሮ፣ መሰረታቸው በነብዩ እና ፓትርያርክ በሆነው በአብርሀም ላይ ነው፣ እንዲሁም፣ የሶስቱም ነብያት የዘር ሀረጋቸው የሚመዘዘው በቀጥታ ከልጆቹ ሲሆን መሀመድ የመጀመሪያ ልጅ ከሆነው የእስማኤል ዝርያ ሲሆን ሙሴ እና እየሱስ ደግሞ ከይስሀቅ ናቸው:: አብርሀም መኖሪያውን በዛሬዋ መካ ከተማ ላይ መሰረተ፣ እናም ሁሉም ሙስሊሞች በጸሎት ጊዜ ፊታቸውን የሚያዞሩበት አቅጣጫ የሆነውን ቃባን ገነባ::


ቃባ ምንድንነው?

በመካ, ሳውዲ አረቢያ

ቃባ የአምልኮ ስፍራ ሲሆን ከአራት ሺህ አመታት በፊት አምላክ አብርሀምንና እስማኤልን ይገነቡት ዘንድ ያዘዛቸው ነው:: ህንጻው የተገነባው ከድንጋይ ሲሆን አብዛኞች በአዳም የተመሰረተ የመጀመሪያው መቅደስ እንደነበር ያምናሉ:: አምላክም የሰው ልጅ በሙሉ ይህን ቦታ እንዲጎበኙ ይጠራቸው ዘንድ አብርሀምን አዝዞታል፣ ወደዚህ መንፈሳዊ ጉዞ የሚያደርጉት እዚህ ቦታ ሲደርሱ “ጌታ ሆይ፣ ላገልግሎት መጥቻለሁ” በማለት ለአብርሀም ጥሪ ምላሽ ይሰጣሉ::


መሀመድ ማነው?

መሀመድ፣ የተወለደው በ570 አመት በመካ ውስጥ ሲሆን፣ በዛን ጊዜ ክርስትና በአውሮፓ እንኳ ስር ሰዶ አልተቋቋመም ነበር:: አባቱ ከመወለዱ በፊት በመሞቱ፣ እናቱም ብዙም ሳትቆይ በመሞቷ ምክንያት ከተከበረው ከቁራይሽ ጎሳ የሆኑት አጎቱ አሳደጉት:: እያደገ ሲሄድም፣ በእውነተኝነቱ፣ በደግነቱ፣ በጨዋነቱ ይታወቅ ነበር፣ ስለዚህም ባለመግባባቶች ጊዜ ችግሮችን በመፍታት ችሎታው ይፈለግ ነበር:: የታሪክ ተመራማሪወችም የተረጋጋ እና በተመስጦ የተሞላ እንደነበር ይገልጹታል::

መሀመድ ፍጹም የሆነ ሀይማኖታዊ ተፈጥሮ የነበረው፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረውን ኢ_ግብረገባዊነት አጥብቆ ይጠላ የነበረ ነው:: ከጊዜ ወደ ጊዜም በጃባል አል ኑር፣ በመካ አቅራቢያ በሚገኘው “የብርሀን ተራራ” አጠገብ በሚገኘው የሂራ ዋሻ ውስጥ በተመስጦ ማሳለፍን ልምድ አድርጎታል::


መሀመድ እንዴት ነብይ እና የአምላክ መልዕክተኛ ሊሆን ቻለ?

የነብዩ መስጊድ፣ መዲና፣ ክበቡ የመኖሪያ ቤቱ የነበረውን እና የተቀበረበትን ስፍራ ያመለክታል::

በ40 አመቱ፣ በተመስጦ ውስጥ እንዳለ፣ በመልዐኩ ገብርኤል አማካኝነት መሀመድ የመጀመሪያውን ራዕይ ተቀበለ:: ይህ ራዕይም፣ ለሀያ ሶስት አመታት የቀጠለ ሲሆን ቁርዐን በመባል ይታወቃል::

ከገብርኤል የሚሰማቸውን ቃላቶች መድገም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እና አምላክ የገለጸለትን እውነት መስበክ እንደጀመረ፣ እሱ እና ጥቂት የነበሩት ተከታዮቹ መራር የሆነ ፈተና ደርሶባቸዋል፣ መከራው እየጸናባቸው ሄዶ በ622 አመት ይሰደዱ ዘንድ የአምላክ ትዕዛዝ ሆነ:: ይህ ክስተትም የ”ሂጅራ” ስደት፣ መካን ትተው 260 ማይል በሰሜን አቅጣጫ ወደአለችው መዲና ከተማ ተጓዙ፣ ይህም የእስልምና ቀን መቁጠሪያ መታሰቢያ ነው::

የብርሀን ተራራ ገብርኤል ለመሀመድ የተገለጸለት ስፍራ

ከብዙ አመታት በኋላም፣ ነብዩ እና ተከታዮቹ ወደ መካ መመለስ ችለዋል፣ ጠላቶቻቸውንም ይቅር በማለት እስልምናን በጽኑ መሰረት ላይ አቋቁመዋል:: ነብዩ በ63 አመቱ ከመሞቱ በፊት፣ አብዛኛው የአረቡ ክፍል ሙስሊም ነበር፣ እንዲሁም ከሞቱ በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ እስልምና በምዕራብ እስከ ስፔን በምስራቅ እስከ ቻይና ተስፋፍቶ ነበር::


የእስልምና መስፋፋት እንዴት በአለም ላይ ተፅዕኖ አደረገ?

ታጅ ማሃል፣ ህንድ፣

ፈጣን እና ሰላማዊ ለሆነው የእስልምና ሀይማኖት መስፋፋት ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ ያልተወሳሰበው የእምነቱ ህግ ተጠቃሽ ነው፣ እስላም በአንድ አምላክ ብቻ እንድናምን የሚያስተምር ነው፤ እንዲሁም ደግሞ በተደጋጋሚ የሚያዝዘው ነገር የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠውን የማገናዘብ እና የማስተዋል ችሎታውን እንዲጠቀም ነው::

በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው የሁይ ሸን መስጊድ::

በጥቂት አመታት ውስጥም፣ ታላላቅ ስልጣኔዎችና ዩኒቨርሲቲወች መስፋፋት ችለዋል፣ ነብዩ እንደተናገረው፣ “እውቀትን መሻት የእያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ግዴታ ነው::” የምስራቁንና የምእራቡን ሀሳብ ማዋሀድ መቻሉ እና ከአሮጌው አስተሳሰብ ላይ አዳዲስ ሀሳቦች መፍለቃቸው፣ በተለያዩ ነገሮች ላይ እመርታ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፤ ከነዚህም ውስጥ በህክምና፣ በሂሳብ፣ በፊዚክስ፣ በጠፈር ምርምር፣ በጂኦግራፊ፣ በኪነ_ህንጻ፣ በጥበብ፣ በስነ ጽሁፍ እንዲሁም በታሪክ ላይ እድገት አሳይቷል:: እንዲሁም ደግሞ ጥልቅ ምርምር በሚጠይቁ አሰራሮች ላይ እንደ አልጀብራ፣ የአረብኛ አሀዞች ላይ እንዲሁም ደግሞ ስለ ዜሮ (ለሂሳብ እድገት ቁልፍ ሚና የነበራት) ጽንሰ ሀሳቦች መፍለቂያ ሆኗል፣ ይህም እውቀት ወደ ማዕከላይ ዘመን አውሮፓ የተሻገረው ከእስላም ነው:: የአውሮፓውያኖች የባህር ላይ አሰሳ እውን እንዲሆን ያደረጉት የተራቀቁ ውስብስብ መሳሪያወች በመገንባታቸው ነው ከእነዚህም ውስጥ አስትሮላብ፣ ኳድራንት እንዲሁም ጥሩ የአሰሳ ካርታ በመኖሩ ነው::


ቁርዐን ምንድን ነው?

ቁርዐን አምላክ በመልዐኩ ገብርኤል አማካኝነት ለነብዩ መሀመድ የገለጸለትን እያንዳንዷን ትክክለኛ ቃላት የያዘ መዝገብ ነው:: መሀመድ በአዕምሮው አስታውሶ ለተከታዮቹ በቃል በማጻፍ ሲሆን፣ ጸሀፍትም በመጽሀፍ አስፍረው፣ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ያረጋገጡት ነው:: ከ114 ምዕራፎቹና፣ ከሱራ አንዲትም ቃል እንኳ ባለፉት ክፍለዘመናት አልተለወጠም፣ ስለዚህ ቁርዐን ከአስራ አራት ክፍለዘመን በፊት በመሀመድ በኩል የተገለጸልን፣ በሁሉም ረገድ ልዩ እና አስገራሚ የሆነ መጽሀፍ ነው::

ይህ የቁርዐን መክፈቻ ምዕራፍ “ፈቲያ” በእስልምና ጸሎት ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ ይይዛል:: የቁርዐን ምሉዕ የሆነውን የያዘ ሲሆን በእያንዳንዱ የጸሎት ወቅት የሚደገም ነው::

ቁርዐን ስለምን ነው?

ቁርዐን፣ አምላክ የገለጸልን የመጨረሻው ቃል፣ የእያንዳንዱ ሙስሊም እምነት እና ተግባር ዋና መሰረቱ ነው:: እንደ የሰው ልጅነታችን ስለሚያስጨንቁን ጉዳዮች ያስረዳል፣ ጥበብ፣ እምነት፣ አምልኮ እና ህግ የሚያስረዳ ቢሆንም በመሰረታዊነት የሚያጠንጥነው ግን በአምላክ እና በፍጥረት መካከል ስላለው ግንኙነት ነው:: እንደዚሁ ሁሉ ስለ መልካም ማህበረሰብ፣ ስለ ግብረ ገብነት እና ስለ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል መምሪያወችን ይሰጣል::


ቅዱሱ የሆኑ ሌሎች መዛግብቶች ይኖራሉን?

አወ፣ ሱና፤ የነብዩ ምሳሌንና ተግባርን ያሰፈረ መጽሀፍ ሲሆን፣ በሙስሊሞች ዘንድ በሁለተኝነት ቅዱስ የሆነ መዝገብ ነው:: ሀዲስ ነብዩ ያደረገውን፣ የተናገረውን፣ ወይም ያረጋገጠውን ያለግድፈት በስነ_ስርዐት ያስተላለፈ ነው:: ሱናን መቀበል የእስልምና ህይወት አንዱ አካል ነው::

ነብዩ ከተናገራቸው ለምሳሌ ያህል

ነብዩ እንደተናገረው:

“ለሌሎች ምህረት ለማያደርጉ ከአምላክ ምህረት አያገኙም”

“ለራሳችሁ የተመኛችሁትን ለወንድማችሁ እስካልተመኛችሁ ማንኛችሁም አማኝ አይደላችሁም”

“ጎረቤቱ ጦሙን እያደረ እርሱ ጠግቦ የሚያድር አማኝ አይደለም”

“እውነተኛ እና ታማኝ ነጋዴ ከነብያት፣ ከቅዱሳን እና ከሰማዕታት ጋር ይመሰላል”

“ሀይለኛነት ሌሎችን የሚዘርር ሳይሆን፣ ግን ሀይለኛ የሚባለው በተናደደ ጊዜ ራሱን የሚቆጣጠር እርሱ ነው::

“አምላክ በአካላችሁና በቁመናችሁ አይዳኛችሁም ግን ልባችሁን መርምሮ ተግባራችሁን አይቶ እንጂ”

“አንድ በመንገድ ላይ የሚጓዝ ሰው ውሀ በጽኑ ጠማው ወደ ውሀ ጉድጓድ በመውረድም፣ ጥሙ እስኪረካ በመጠጣት ተመለሰ፣ ከዚያም ምላሱን አውጥቶ የሚያለክልክ ውሻ ተመለከተ፣ ውሻውም ጥሙን ለማስታገስ የረሰረሰ አመድ ይልስ ነበር:: ሰውየውም ውሻውን ባየው ጊዜ የራሱ ጥም የተሰማውን ያህል የውሻውን ጥም አሰበ በድጋሚ ወደ ጉድጓድ በመሄድም ውሀ በጫማው በመሙላት ይጠጣው ዘንድ ለውሻው ሰጠው:: አምላክም ለዚህ በጎ ተግባሩ ሀጢያቱን ይቅር አለው::” ነብዩንም “የአምላክ መልዕክተኛ ሆይ፣ ለእንስሳት ለምናደርገው ደግነት እንሸለም ይሆን?” በማለት ሲጠይቁት፣ እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ “ ለፍጥረት ሁሉ ለምታደርጉት ደግነት ሽልማት ይኖራችኋል::”

ከቡካሪ፣ ሙስሊም፣ ቲርሚዲህ እና ባይሀቂ የሀዲስ ስብስቦች::

የእስልምና “አምስቱ” ምሰሶዎች እነማን ናቸው?

እምነት፣ ጸሎት፣ እርዳታን ለሚሹ ተቆርቋሪነት፣ ራስን_ማንጻት እና ለሚቻላቸው ወደ መካ መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ የእስልምና ህይወት መሰረት ናቸው::

1. እምነት

በኢስታንቡል፣ በኦቶማን ቶፕካፒ(ከብዙ ቅርሶች መካከል፣ የነብዩ የራስ ላይ ጥምጣም ይገኝበታል) ቤተመንግስት መግቢያ ላይ የተፃፈ ሻህዳ::

“ከአምላክ በቀር አምልኮ የሚገባው ሌላ አምላክ የለም እና መሀመድ የእርሱ መልዕክተኛ ነው::”

ይህ የእምነት አዋጅ ሻህዳ ተብሎ ይጠራል፣ አማኝ የሆነ ሁሉ ሊደግመው የሚችል ቀላል ቀመር ነው:: የመጀመሪያው ከፍል፣ በአረብኛ: ላ ኢላህ ኢላ ላህ – “ከአምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም”፤ ኢላህ(አምላክ) እኛ በአምላክ ቦታ የምንመስለውን ሁሉ ይወክላል፣ አምላክ ፣ ሀብትን፣ ሀይልን እናም ሌሎችን፣ በመቀጠል የሚመጣው ኢላ ላህ: “ከአምላክ በቀር”፣ የፍጥረት ሁሉ መሰረት::

የሻህዳ ሁለተኛው ክፍል መሀመዱን ራሱሉላህ፣ “መሀመድ የአምላክ መልዕክተኛ ነው::” እንደ እኛ ሰው በሆነ የመመሪያችን መልዕክት መጣልን::

2. ፀሎት

በቀን ውስጥ ለአምስት ጊዜ መፈጸም ያለበት ጸሎት፣ ሰላት ይባላል፤ ይህም አምላክን እና ምዕመኑን በቀጥታ የሚያገናኝ ነው:: በእስላም ውስጥ ምንም አይነት የስልጣን ተዋረድ እና ካህን የለም፣ ስለዚህ ጸሎቱ የሚመራው ቁርዐንን በሚያውቅ በተማረ ሰው ሲሆን፣ በተሰበሰበው ምዕመን የሚመረጥ ይሆናል:: አምስቱ ጸሎቶችም ከቁርዐን ጥቅሶችን የያዙ ሲሆን፣ በራዕይ በተገለጸበት ቋንቋ፣ በአረብኛ የሚደገሙ ይሆናል፣ የግል ጸሎት ግን በራሱ ቋንቋ መደረግ ይችላል::

የፀሎት ሰዐታትም ንጋት ላይ፣ ረፋድ፣ ከሰዐት በኋላ፣ በጸሀይ ግብዐት(ጸሀይ ስትጠልቅ) እንዲሁም በምሽት ላይ ይደረጋል፣ ይህም የሙሉ ቀኑን ዑደት በጠበቀ መልኩ ይሆናል:: በመስጊድ ከሌሎች ጋር በመሆን አምልኮ መፈጸም የተሻለ ቢሆንም፣ ሙስሊም በማንኛውም ቦታ መጸለይ ይችላል፣ ለምሳሌ መስክ ላይ፣ ቢሮ ውስጥ፣ በፋብሪካ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መጸለይ ይችላል:: ሙስሊም አለማትን የሚጎበኙ ሁሉ የፀሎት ተግባሩ ከእለት ተዕለት የህይወት ተግባር ጋር ባለው ቁርኝት ይመሰጣሉ::

ከአቢኲይ መስጊድ
የፀሎት ጥሪ፣ ኒው ሜክሲኮ ፣ አሜሪካ::

የፀሎት ጊዜ ጥሪ ትርጓሜ:

አምላክ ታላቅ ነው፣ አምላክ ታላቅ ነው::
አምላክ ታላቅ ነው፣ አምላክ ታላቅ ነው::.
ከአምላክ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ምስክር እሆናለሁ::
ከአምላክ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ምስክር እሆናለሁ::
መሀመድ የአምላክ መልዕክተኛ መሆኑን ምስክር እሆናለሁ::
መሀመድ የአምላክ መልዕክተኛ መሆኑን ምስክር እሆናለሁ::
ወደ ፀሎት ኑ! ወደ ጸሎት ኑ!
ወደ ስኬት ኑ(በዚህኛው እና በወዲያኛውም ቢሆን)
ወደ ስኬት ኑ
አምላክ ታላቅ ነው:: አምላክ ታላቅ ነው::
ከአምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም::

3. ዘካት

ዘካት በማህበረሰቡ ዘንድ ጤናም የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር ያደርጋል:: ካይሮ::

በእስልምና በጣም ጠቃሚ ከሆኑት መርሆች አንዱ ሁሉም ነገር የአምላክ ነው የሚለው ነው፣ እናም ሀብትም ቢሆን እንኳ በሰው ልጅ በታማኝነት የሚቀመጥ ይሆናል:: ዘካት የሚለው ቃል በራሱ “መንጻት” እና “ማደግ” የሚሉ ትርጉሞች ያሉት ነው:: ካለን ሀብት ላይ የሆነ ድርሻ ለሚያስፈልጋቸው ስንመድብ ንብረታችን፣ የነፃ ይሆናል፣ እናም ልክ እንደ አላስፈላጊ የዕፅዋት ዝንጣፊ፣ ከሀብት ላይ ቀንሶ መስጠት አዲስ እድገትን ያመጣል::

እያንዳንዱ ሙስሊም የራሱን ወይም የራሷን ዘካት ያሰላሉ፤ በአብዛኛው ይህን ሲያደርጉ በአመት ካላቸው ሀብት ላይ ሁለት ከግማሽ የሚሆነውን በመክፈል ነው::

ሀይማኖተኛ ሰው የሚችለውን ያህል ወይም የምትችለውን ያህል እንደ ሰደቃ ማድረግ ይችላል፣ ይህ ሲሆን ግን በሚስጢር ቢሆን ይመረጣል:: ምንም እንኳ ይህ ገለጻ እንደ “በጎ ፈቃድ ልግስና” በመባል ቢተረጎምም ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ነው:: ነብዩ እንደተናገረው “ወንድማችሁን ስታገኙ እንኳ በደስታ ፊት ከተቀበላችሁት ስለልግስና ቁጥር ነው::”

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ፡፡

ነብዩ እንደተናገረው፤ “መመጽወት የእያንዳንዱ ሙስሊም ግዴታ ነው::” እንዲህም ብለው ሲጠይቁት: “ሰውየው ምንም ከሌለውስ” በማለት ሲጠይቁት: “በራሱ እጅ ለራሱ ጥቅም መስራት እና ከደመወዙ መጥኖ መመጽወት ይገባዋል” በማለት መልስ ሰጥቷል:: ቀጥለውም “መስራት የማይችል ከሆነስ?” በማለት ሲጠይቁት “ድሆችን እና ረዳት የሚሹትን መርዳት ይኖርበታል::” በማለት መልሶላቸዋል:: እነርሱም ደግመው “ይህንን እንኳ ማድረግ የማይቻላቸው ከሆነስ?” በማለት ሲጠይቁት “ሌሎች መልካም ያደርጉ ዘንድ ማነሳሳት አለበት” በማለት መልሶላቸዋል፣ እነርሱም “ይህን ማድረግ ከተሳነውስ?” በማለት ሲጠይቁት “ራሱን ከእርኩሰት መጠበቅ ይገባዋል፣ ይህም ራሱ ልግስና ነው::” በማለት መልሶላቸዋል::

4.ፆም

በእያንዳንዱ አመት በረመዳን ወራት፣ ሁሉም ሙስሊም ከንጋት እስከ ምሽት ይፆማሉ፣ ከምግብ፣ ከመጠጥ እንዲሁም ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ይቆጠባሉ:: ለህሙማን፣ ለአቅመ ደካሞች፣ በጉዞ ላይ ላሉት፣ እንዲሁም ለአራስ ሴቶች ወይም ለነፍሰ ጡሮች ጾሙን እንዲያቋርጡ ይፈቀድላቸዋል፣ በኋላ ላይም እኩል የጾም ቀናትን ለራሳቸው መድበው መጾም ይችላሉ:: ለመጾም አቅማቸው የማይፈቅድ ከሆነ፣ በሚያሳልፏት በእያንዳንዱ ቀን የእነሱን እርዳታ የሚሻውን ይመግቡ ዘንድ ግዴታ አለባቸው:: ልጆች መጾም (እና ፀሎት መከታተል) የሚጀምሩት በወጣትነታቸው ጊዜ ቢሆንም፣ አብዛኞች ገና ከልጅነታቸው ይጀምራሉ::

ጾም ለጤና ጥቅም የሚሰጠን ቢሆንም፣ ራስን ለማጥራት ዋነኛ መንገድ ነው:: ራስን ከአለማዊ ምቾቶች ዞር ማድረግ፣ ለአጭር ጊዜ ቢሆን እንኳ፣ የሌሎችን መራብ እውነተኛ ስሜት ይረዱበታል እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወት እድገትን ያገኛሉ::

5. ሀጂ ማድረግ

ሀጂ አድራጊወች በመካ መስጊድ ላይ ጸሎት ሲያደርጉ

በየአመቱ ወደ መካ የሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ “ሀጂ” በገንዘብም ሆነ በአካላዊ አቋም ማድረግ ለሚችሉት ብቻ ግዴታ የሆነ ነው:: የሆነው ሆኖ፣ በየአመቱ ከሁለት ሚሊየን ህዝቦች በላይ ከእያንዳንዷ የአለም ጫፍ ወደ መካ ይህንን ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን ከተለያዩ ሀገር የመጡት ሰወች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ እድሉን የሚፈጥር ነው:: መካ ሁልጊዜም ቢሆን በጎብኝወች የተሞላች ብትሆንም፣ አመታዊው ሀጂ የሚጀምረው በእስልምና የዘመን አቆጣጠር በአስራ ሁለተኛው ወር ነው (የዘመን አቆጣጠሩ ጸሀይን ሳይሆን፣ ጨረቃን መሰረት ያደረገ ነው፣ ስለዚህ ሀጂ እና ረመዳን አንዳንዴ በክረምት አንዳንዴ ደግሞ በበጋ ሊሆን ይችላል::) ይህን ጉዞ የሚያደርጉት ሁሉ ልዩ የሆነ ልብስ ያደርጋሉ፣ የሚለብሱትም ርካሽ ሸማ ልብስ ሲሆን ማንኛውንም አይነት የመደብ እና የባህል ልዩነቶችን የሚያስወግድ ይሆናል፣ ስለዚህም ሁሉም በአምላክ ፊት እኩል ሆኖ ይቀርባል::

የሀጂ አድራጊወች ድንኳን::

የሀጂ ስርዐቱም፣ መሰረቱ ከአብርሀም ሲሆን፣ ቃባውን ሰባት ጊዜ መዞርን ያካትታል እንዲሁም ሀጋር ውሀ ፍለጋ እንዳደረገችው በሳፋ እና በማርዋ ተራሮች መካከል ሰባት ጊዜ መመላለስን ይጨምራል:: በመቀጠልም ተጓዞች አንድ ላይ በመሆን ከአርፋ በታች ባለው ሰፊ ሜዳ ላይ በመሆን የአምላክን ይቅርታ በጸሎት ይጠይቃሉ፣ ይህም የመጨረሻውን የእለተ ምጽዐት ቅድመ ምልከታ እንደሆነ ይታሰባል::

በቀድሞወቹ ክፍለ ዘመናት ሀጂ ማድረግ እጅግ ከባድ ነገር ነበር፣ ዛሬ ላይ ግን፣ ሳዑዲ አረቢያ ለሚሊዮኖች ውሀ፣ ዘመናዊ መጓጓዣ፣ እንዲሁም ከዘመኑ ጋር የረቀቁ የህክምና ተቋማት ማቅረብ የሚያስችል አቅም ያላት ናት::

የሀጂ መጠናቀቂያም በክብረ በአል ይታወሳል ይህም ኢድ አል አድሀ ይባላል፣ በጸሎት እና በመላው አለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ ስጦታወችን በመለዋወጥ ይከበራል:: ይህ እና ኢድ አል ፈጥር፣ የረመዳን ጾም ማብቂያ የሚታወስበት ቀን፣ በሙስሊም አቆጣጠር ታላቅ ክብረ በአሎች ናቸው::


እስልምና ከሌሎች እምነቶች ጋር ይቸቻላልን?

ቅዱስ ቁርዐን እንዲህ ይላል:

“ከነዚያ በሀይማኖት ካልተጋደላችኋቸው ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ (ከሀዲዎች) መልካም ብትውሉላቸውና ወደነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና::”

(ቅዱስ ቁርዐን 60:8)

የእስልምና ህግ አንዱ ተግባር የአናሳወችን መብት ማስጠበቅ ነው፣ ለዚህ ነው ሙስሊም ያልሆኑ የአምልኮ ቦታወች በመላው የእስላሙ አለም ውስጥ ሊያብቡ የቻሉት:: የእስልምናን እና የሌሎችን እምነቶች መቻቻል በማስመልከት ታሪክ በርካታ መዛግብትን ያቀርባል፣ ለምሳሌ በ634 አመት ካሊፋ ኦማር እየሩሳሌምን በተቆጣጠረ ጊዜ፣ እስልምና በከተማዋ ውስጥ ላሉት ሀይማኖቶች በሙሉ የአምልኮ ነጻነትን ሰጥቷቸዋል::

እንዲሁም ደግሞ የእስልምና ህግ ሙስሊም ያልሆኑ አናሳ ማህበረሰቦች በራሳቸው የተዘጋጀ የቤተሰብ ህጋቸውን የሚተገብሩበት ፍርድ ቤት ያቋቁሙ ዘንድ ይፈቅዳል::


ሙስሊሞች ስለ እየሱስ ምን ያስባሉ?

ሙስሊሞች እየሱስን ያወድሱታልም ያከብሩታልም፣ እንዲሁም ዳግም ምፅዐቱን ይጠብቃሉ:: አምላክ ወደ ሰው ልጆች ከላካቸው ታላላቅ መልዕክተኞች እንደ አንዱ የሚመለከቱት ነው:: ሙስሊሞች እንዲሁ በደፈናው “እየሱስ” በማለት አይገልጹትም ግን “ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና” የሚለውን ሀረግ በማከል እንጂ:: ቁርዐን (“ማርያም” በሚለው የቅዱስ ቁርዐን ክፍል ውስጥ) በድንግልና እንደተወለደ ያረጋግጣል፣ እንዲሁም ማርያም ከሴቶች ሁሉ ንጽህት እንደሆነች ይገልጻል:: ቁርዐንም የየምስራች ብስራቱን እንደሚከተለው ገልጾታል::

“መላእክትም ያሉትን (አስታውስ) መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሽ አነጻሽም በአለማት ሴቶችም ላይ መረጠሽ:: መላዕክት ያሉትን (አስታውስ) መርየም ሆይ! አላህ ከርሱ በሆነው ቃል ስሙ አልመሲህ ዒሳ የመርየም ልጅ በዚህ አለምና በመጨረሻውም አለም የተከበረ ከባለሟሎችም በሆነ (ልጅ) ያበስርሻል፤ በህጻንነቱና በከፈኒሳነቱ ሰወቹን ያነጋግራል ከመልካሞቹም ነው (አላት)::

“ጌታየ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስሆን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች ነገሩ እንደዚህሽ ነው አላህ የሚሻውን ይፈጥራል አንዳችን ባሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል ወዲያውኑም ይሆናል አላት::”

(ቅዱስ ቁርዐን 3:42-47)

የእየሱስ ተአምራዊ ውልደት አዳምን ያለአባት ወደ አለም እንዳመጣው ያለ ተመሳሳይ ሀይል ነው::

አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው ከአፈር ፈጠረው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ሁን አለው ሆነም::

(ቅዱስ ቁርዐን 3:59)

እየሱስም በመልዕክተኛነት ተልዕኮው የተለያዩ ተዐምራትን ፈጽሟል:: ቅዱስ ቁርዐንም ያን እንዲህ ብሎ ይነግረናል::

እኔ ከጌታየ ዘንድ በተዐምር መጣኋችሁ እኔ ለእናንተ ከጭቃ እንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ በእርሱም እተነፍስበታለሁ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል:: በአላህም ፈቃድ ዕውር ሆኖ የተወለደን ለምጸኛንም አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ::

(ቅዱስ ቁርዐን 3:49)

መሀመድም ሆነ እየሱስ ከእነርሱ በፊት በነበሩት መልዕክተኞች የመጣውን መሰረታዊ የእምነት ህግጋት ሊቀይሩ አልመጡም፣ ግን ሊያድሱት እና ሊያረጋግጡት እንጂ:: በቅዱስ ቁርዐንም እየሱስ ለምን እንደመጣ እንዲህ ተዘግቧል::

ከተውራትም ከኔ በፊት ያልለውን ያረጋገጥሁ ስሆን የዚያንም በናንተ ላይ እርም የተደረገውን ከፊል ለናንተ እፈቅድ ዘንድ (መጣኋችሁ) ከጌታችሁም በሆነ ታምር መጣሁዋችሁ አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም::

(ቅዱስ ቁርዐን 3:50)

ነብዩ መሀመድም እንደተናገረው::

ማንም ይሁን ማን አንድ እርሱ ብቻ ከሆነ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ የሚያምን፣ መሀመድ መልዕክተኛው እንደሆነ፣ እየሱስም የአምላክ አገልጋይ እና መልዕክተኛ እንደሆነ፣ የአምላክ ቃልም በማርያም ላይ ተንፍሶ መንፈሱ ከእርሱ የወጣ የተገኘ፣ እንዲሁም ገነት እና ገሀነም እውነት የሆኑ፣ ወደ ገነትም አምላክ እንደሚቀበላቸው፤

(ቡካሪ ከ ሀዲስ)

በሙስሊሞች ዘንድ ቤተሰብ በጣም አስፈላጊ ለምን ሆነ?

ቤተሰብ በእስልምና ማህበረሰብ ውስጥ ዋና መሰረት ነው:: በተረጋጋ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ሰላም እና ደህንነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፣ ለተከታዩች የመንፈሳዊ ጥንካሬ እድገት በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ ይታመናል:: አንድ ማህበረሰብ በስምምነት የሚኖረው በዝምድና የተያያዘ ቤተሰብ ሲመሰርት ነው፣ ልጆች ውድ ሀብት ናቸው፣ እናም ከስንት አንዳንዶቹ በስተቀር እስኪያገቡ ድረስ ቤታቸውን ለቀው አይሄዱም::


ስለ ሙስሊም ሴቶችስ?

እስልምና ባለትዳርም ሆነ ያላገቡ ሴቶችን የሚያየው፣ እንደ አንድ ግለሰብ የራሷ የሆነ መብት እንዳላት፣ የራሷ የሆነ ገቢ እና የምታዝዝበት ንብረት ሊኖራት መብት እንዳላት ነው:: በጋብቻ ወቅት የሚመጣላት ጢሎሽም ለራሷ የግል መጠቀሚያዋ ነው፣ እንዲሁም ደግሞ መጠሪያዋ በባለቤቷ ስም ሳይሆን በአባቷ ስም እንደሆነ ሳይለወጥ ይቀጥላል::

ሁሉም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የሰውን ቀልብ በማይሰርቅ መልኩ የሚያስከብር አለባበስ ይለብሱ ዘንድ ይጠበቃል፤ በአንዳንድ ሙስሊም ሀገሮች ዘንድ ያለው የሴቶች ባህላዊ አለባበስ የሚያንጸባርቀው በአካባቢው ያለውን ባህል ነው::

የአምላክ መልዕክተኛም እንደተናገረው:

“ከአማኞች መካከል በእምነት ፍጹም የቀናው ለሚስቱ ደግ እና ባለ ጥሩ ምግባር የሆነው እርሱ ነው::”


ሙስሊም ከአንድ በላይ ሚስት ሊኖረው ይችላልን?

የእስልምና ሀይማኖት የተገለጸው ለሁሉም ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም እጅግ የተለያዩ ማህበረሰባዊ መስፈርቶችን ያገናዘበ ነው:: ያለበቂ ምክንያትና ዋስትና ሁለተኛ ሚስት ማግባት የሚከለክል ቢሆንም መብት አለው:: ቅዱስ ቁርዐን እንደሚያትተውም፣ ባልተቤትየው ሁኔታወችን በፍትሀዊ መንገድ ካገናዘበ ብቻ መሆን አለበት::


የእስልምና ጋብቻ እንደ ክርስቲያኖች ጋብቻ ነው?

የሙስሊም ጋብቻ “በቁርባን” የሚከወን ሳይሆን ግን ቀለል ያለ፣ በጥንዶች መካከል በሚደረግ ህጋዊ ስምምነት የሚደረግ እና የመሰላቸውን መስፈርት የማካተት መብት ያላቸው ነው:: የጋብቻ አፈፃፀም ባህሎችም ከሀገር ሀገር የተለዩ ናቸው:: በዚህ ምክንያትም፣ ፍቺ የተለመደ ነገር አይደለም፣ ቢሆንም ግን የመጨረሻው መፍትሄ ከሆነ አይከለከልም:: እንደ እስልምና ህግጋት፣ ማንም ሙስሊም ሴት ከፈቃዷ ውጭ የሆነን ታገባ ዘንድ አትገደድም፣ ቤተሰቦቿ እንዲሁ የእድሜ እኩያዋ የሆነና ይመጥናታል ብለው የሚያስቡትን ልጅ ያመላክቷታል::


ሙስሊሞች እንዴት በዕድሜ የገፉ ሰወችን ይንከባከባሉ?

በእስልምና አለም በዕድሜ የገፉ ሰወች ተነጥለው የሚኖሩበት ቤት የለም:: በዚህ በህይወታቸው አስቸጋሪ ወቅት የአንድን ቤተሰብ መንከባከብ ክብር እና ምርቃትን የሚያስገኝ እንደሆነ ይታመናል፣ እንዲሁም ለመንፈሳዊ እድገት እንደ ትልቅ አጋጣሚ የሚታይ ነው:: አምላክም ለቤተሰቦቻችን እንድንጸልይላቸው ብቻ አይደለም የጠየቀን፣ ግን ገደብ የለሽ ርህራሄ እንድናሳያቸው ነው፣ እኛ አቅም የለሽ ህጻናት እንደነበርን ይንከባከቡን እንደነበር በማስታወስ እናደርገው ዘንድ ነው:: በተለይ ደግሞ እናቶች ይከበራሉ፣ነብዩ “ጀነት በእናቶች እግር ስር ነች” በማለት አስተምሯል:: በሽምግልና ዘመናቸውም፣ ሙስሊም ወላጆች ምህረት በተሞላበት፣ በደግነት እና ፍጹም በሆነ ቸርነት ክብካቤ ይደረግላቸዋል::

በእስልምና፣ ወላጆችን መንከባከብ ከመጸለይ በማስቀጠል ያለ ግዴታ ነው፣ እንዲሁም መጠበቁ የራሳቸው መብት ነው:: ያለእነርሱ ጥፋት ሽማግሌወች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜ ቁጣቸውን መግለጽ እንደ ንቀት ይቆጠርባቸዋል::

ቅዱስ ቁርዐን እንደተናገረው:

“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ በአንተ ዘንድ ሆነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው አትገላምጣቸውም ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው:: ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፤ ጌታየ ሆይ በህጻንነቴ (በርህራሄ) እንዳሳደጉኝ እዘንላቸውም በል::”

(ቅዱስ ቁርዐን 17:23-24)

ሙስሊሞች ሞትን እንዴት ይመለከቱታል?

እንደ አይሁዳዊያን እና ክርስቲያኖች ሁሉ፣ ሙስሊሞች የአሁነኛው ህይወት ለቀጣዩ ዘላለማዊ ህይወት መዘጋጃ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ:: መሰረታዊ የእምነቱ አናቅጾችም የፍርድ ቀን፣ ትንሳኤን፣ ገነትን እና ገሀነምን ያካትታሉ:: አንድ ሙስሊም ሲሞት/ ስትሞት፣ እርሱ ወይም እርሷ ይታጠባሉ፣ በተለምዶ የቤተሰብ አባል ይህን ያደርጋል፣ በንጹህ ነጭ ጨርቅ ይጠቀለላሉ፣ እናም ያልተንዛዛ ጸሎት ተደርጎ በዛው ቀን ቢቀበሩ ይመረጣል:: ሙስሊሞች ይህ ለዘመዶቻቸው ያደረጉት የመጨረሻ አገልግሎት እንደሆነ ያስባሉ፣ እናም በምድር ላይ ያላቸውን ቆይታ ምን ያህል አጭር እንደሆነ የማስታወስ እድሉን ይፈጥርላቸዋል:: ነብዩ እንዳስተማረው፤ ከሞት በኋላ እንኳን የሚቀጥሉ እና የሚረዱን ሶስት ነገሮች አሉ እነዚህም፤ ለተቸገሩት የለገስነው፣ ሌሎችን ያስተማርነው እውቀት እንዲሁም በእነርሱ ስም ሀጢያት በሌለበት ልጅ የተደረገላቸው ጸሎት ናቸው::


እስልምና ስለ ጦርነት ምን ይላል?

እንደ ክርስትና ሁሉ፣ እስልምናም ራስን ለመከላከል የሚደረግ ትግልን ይፈቅዳል ማለትም፣ ሀይማኖትን ለመከላከል፣ ወይም ደግሞ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ለመርዳት:: በማጥቃት ዘመቻም ጠንካራ ህግጋት ያሉት ነው እነዚህም ሰላማዊ ዜጎች ላይ አደጋ እንዳይጣልባቸው የሚከለክል እንዲሁም አዝመራ ማውደምን የሚከለክል፣ ዛፎችን እና የቤት እንስሳትን ለጥፋት መዳረግን አጥብቆ የሚከለክል ነው:: ሙስሊሞች እንደሚመለከቱትም፣ መልካም ሰወች ራሳቸውን ለትክክለኛ ምክንያት መስዋትነት ለመክፈል ካልተዘጋጁ ኢ_ፍትሀዊነት በአለሙ ላይ ይሰፍናል:: ቅዱስ ቁርዐን እንደሚለውም

እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሀዲዎች) በአላህ መንገድ ተጋደሉ ወሰንንም አትለፉ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና::

(ቅዱስ ቁርዐን 2:190)

ወደ እርቅም ቢያዘነብሉ ወደ እርሷ አዘንብል በአላህም ላይ ተጠጋ እነሆ እርሱ ሰሚ አዋቂ ነውና::

(ቅዱስ ቁርዐን 8:61)

ስለዚህ ጦርነት የመጨረሻው መፍትሄ የሚሆነው በቅዱሱ ህግጋት የተቀመጠውን ጥሶ ከመጣ ነው:: ጂሀድ የሚለው ቃል ትርጉሙም “ትግል” ማለት ነው፣ ሙስሊሞች ሁለት አይነት የጂሀድ አይነቶች እንዳሉ ያምናሉ:: ሌላኛው “ጂሀድ” ውስጣዊ ትግል ሲሆን ውስጣዊ ሰላምን ከማግኘት አኳያ እያንዳንዱ ራስን አግዝፎ በመመልከት ላይ የሚያውጀው ትግል ነው::


ስለ ምግብ ምን ይላል?

አይሁዶች እና ቀደምት ክርስቲያኖች ይከተሉት ከነበረው የአመጋገብ ህግጋት ይበልጥ የቀለለ ቢሆንም፣ ሙስሊሞች የሚከተሉት ደምብ የአሳማ ስጋን ከመብላት ወይም ማንኛውንም አይነት አልኮል መጠጥ ከመጠጣት የሚከለክል ነው:: ነብዩ እንዳስተማረው “አካላችሁ በእናንተ ላይ ስልጣን አለው”፣ እናም ለጤና ተስማሚ ምግብ መመገብ እና ጤናማ የሆነ ህይወትን መምራት እንደ ሀይማኖታዊ ግዴታወች የሚታዩ ናቸው::

ነብዩ እንደተናገረውም:

“አምላክን ጽንዐት(የእምነት) እና ደህንነትን ጠይቁት፣ ከጽንዐታችሁ ባሻገር፣ ማንም ከጤና የተሻለ ስጦታ አልተሰጠውም!” በማለት ተናግሯል::


እስልምና እንዴት ለሰብዐዊ መብት ጠበቃ ይቆማል?

በቅዱስ ቁርዐን ላይ የማገናዘብ ነጻነት በግልጽ ተቀምጧል: “በሀይማኖት ማስገደድ የለም::”

(ቅዱስ ቁርዐን 2:256)

በእስላማዊ ሀገራት ላይ ያሉ ዜጎች በሙሉ ሙስሊም ሆኑም አልሆኑም ህይወታቸው እና ንብረታቸው በሙሉ ይከበርላቸዋል::

ዘረኝነት በሙስሊሞች ዘንድ ቦታ የማይሰጠው ሲሆን፣ ቅዱስ ቁርዐን ስለሰው ልጆች እኩልነት በሚከተሉት ቃላቶች ገልጾታል

እናንተ ሰወች ሆይ እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው አላህ ግልጽን አዋቂ ውስጥንም አዋቂ ነው::

(ቅዱስ ቁርዐን 49:13)

እስልምና በአሜሪካ ውስጥ

ኒው ሜክሲኮ፣ አሜሪካ::

ስለ አሜሪካ ሙስሊሞች አጠቃሎ መግለጽ ባይቻልም፣ ሀይማኖታቸውን የለወጡ፣ ፈልሰው የመጡት፣ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ ዶክተሮች፤ እኒህ ሁሉ ለአሜሪካ ወደፊት የበኩላቸውን አሻራ የሚያሳርፉ ቢሆኑም፤ ይህ ውስብስብ ማህበረሰብ በአንድ እምነት የተጣመረ ነው፣ ይህም በሀገሪቱ በሚገኙት በሺህ በሚቆጠሩ መስጊዶች የጸና ነው::

ሙስሊሞች በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ውስጥ ነበሩ:: በአስራስምንተኛው ክፍለዘመን በሺወች የሚቆጠሩ የነበሩ ሲሆን፣ በሰፋፊ እርሻወች ላይ በባርነት ይሰሩ የነበሩ ናቸው:: እኒህ ቀደምት ማህበረሰቦች ከማንነታቸው እና ከቤተሰባቸው ላይ የተቆራረጡ ስለነበሩ፣ በጊዜ ሂደት የእስልምና ማንነታቸውን እያጡ ሄደዋል:: ዛሬ ላይ ግን በርካታ አፍሪካ አሜሪካዊ ሙስሊሞች በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ጠቃሚ የሆነ ሚና በመጨዋት ላይ ይገኛሉ::

በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን፣ በርካታ የአረብ ሙስሊሞች ፈልሰው የገቡ ሲሆን፣ በትላልቅ የኢንዱስትሪ ስፍራዎች ላይ መኖሪያቸውን በማድረግ በኪራይ ቤቶች ውስጥ አምልኳቸውን ይፈጽሙ ነበር:: በሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በመቶ ሺወች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከምስራቁ የአውሮፓ ክፍል ጎርፈው የገቡበት ጊዜ ነበር:: የመጀመሪያው የአልባንያኖች መስጊድም በ1915 እኤአ በ ማይኔ ውስጥ ተከፈተ፤ ሌሎችም እንዲሁ አከታትለው ተከፍተዋል፣ እንዲሁም የፖሊሽ ሙስሊም ማህበረሰብ በብሩክሊን ውስጥ በ 1928 እኤአ መስጊድ ከፍተዋል::

የእስልምና ባህል ማዕከል፣ ዋሽንግቶን ዲሲ::

በ1947 እኤአ በፕሬዘዳንት ትሩማን የስልጣን ዘመን የዋሽንግቶን የእስልምና ማዕከል የተከፈተ ሲሆን፣ በርካታ ሀገር አቀፍ ድርጅቶች ተቋቁመዋል:: በተመሳሳይ ጊዜ ህይወታቸው በእስልምና የተቀረጸ በርካታ ማህበረሰቦች የተቋቋሙበት ወቅት ነበር:: እስከ ቅርብ ጊዜም፣ አብዛኞቹ የእነዚህ ቡድን አባላት በሙስሊም ትክክለኛ እምነት ውስጥ የገቡ ናቸው:: ዛሬ ላይ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሙስሊሞች በአሜሪካ ይገኛሉ::


የሙስሊሙ አለም

በሄራት፣ አፍጋኒስታን፣ የታላቁ መስጊድ ቅፅር::

በአለም ላይ ያለው ሙስሊም ህዝብ ወደ አንድ ቢሊዮን ገደማ ሲሆን፤ 30% የሚሆነው ከህንድ በታች ባለው አህጉራተ አለም የሚኖር ሲሆን፣ 20% ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ 17% በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ 18% በአረቡ አለም፣ 10% በቀድሞ የሩስያ ግዛት በነበሩትና በአሁና ሩስያ እና ቻይና የሚገኝ ሲሆን:: በቱርክ፣ ኢራን እንዲሁም በአፍጋኒስታን 10% የሚሆነውን አረብ ያልሆኑ የመካከለኛው ምስራቅን ያካትታሉ:: ደቡብ አሜሪካና አውስትራሊያን ጨምሮ ሙስሊሞች በሁሉም አካባቢ በትንሽ ቁጥር የሚገኙ ቢሆንም፣ በቀደምት የሩስያ ግዛቶች እና በአሁኗ ሩስያ፣ በህንድ እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ በርከት ብለው ይገኛሉ:: በአሜሪካ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሙስሊሞች ይገኛሉ::

እናንተ ሰወች ሆይ እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው አላህ ግልጽን አዋቂ ውስጥንም አዋቂ ነው::

(ቅዱስ ቁርዐን 49:13)
የአል አዝሀር የዩንቨርሲቲ መስጊድ ከ969 አመት ጀምሮ የመማሪያ ማዕከል በመሆን አገልግሏል::
ተማሪወችም ከመላው የሙስሊሞ አለም ይሰባሰባሉ::
ኢራን | ማሊ
መስጊድ – አስመራ ኤርትራ.
የመን (ንግሥት Sheiba ዘ ምድር.)